ስለ ነቢዩ (ሱ.አ.ወ)ትሕትና እና አዳባቸው
ከማንም ሰው ይበልጥ አዛኝ ፣ከሁሉም ይበልጥ ባልደረቦቻቸውን አክባሪ፣ የተቀመጡበት ቦታ ከጠበባቸው እንዲሰፋ አድራጊ፣ ማንኛውንም ሰው በሚያገኙት ጊዜ አስሰላሙ አለይኩም በማለት የሚጀምሩ ነበሩ፡፡አንድን ሰው በእጃቸው ከጨበጡት የጨበጡት ሰው ራሱ እጁን እስካልሰበሰበ ድረስ እሳቸው እጃቸውን አይሰበስቡም ነበር ነቢዩ ሙሀመድ ለየት ያለ የሆነ ትሕትና(ተዋዱዕ) ባለቤት ነበሩ፡፡ ሰዎች ከተቀመጡበት ሲደርሱ እጫፍ ላይ ይቀመጡ ነበር እንጂ ሰዎችን አስነስተዉ አይቀመጡም ነበር፡፡በዚህ ነገር ላይ ሰዎችንም ያዙ ነበር፡፡ለተቀመጡት ሰዎች ሁሉ ድርሻቸውን ይሰጧቸው ነበር ፡፡ ከነቢዩ ጋር የተቀመጠ ሰው እንደርሱ ነቢዩ የሚያከብሩት ሰው ይገኛል ብሎ አያስብም ነበር፡፡ አንድ ሰው ከእርሳቸው ጋር ከተቀመጠ ይህ ሰው ካልቆመ በስተቀር እርሳቸው አይቆሙም ነበር፡፡ በጣም አሰቸኳይ ነገር ካጋጠማቸው ግን ፍቃድ በመጠየቅ ይቆማሉ፡፡ ነቢዩ ለራሳቸው ክብር ሰው ከመቀመጫው ተነስቶ መቆሙን ይጠሉ ነበር፡፡ አነስ ኢብኑ ማሊክ እንዲህ ብለዋል ‹‹ከአላህ መልእክተኛ ይበልጥ ባልደረቦቻቸው ዘንድ የተወደደ ሰው አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ነቢዩ መምጣታቸውን ሲያዩ ተነስተው ለነቢዩ አይቆሙም ፡፡ይህም ነቢዩ ለራሳቸው ክብር ሰው ከመቀመጫው ተነስቶ መቆሙን እንደሚጠሉ ስለሚያውቁ ነው፡፡ (አህመድና ቲርሚዚ የዘገቡት ሐዲስ) (እንግዳ የመጣበት ሰው እንግዳን ለመቀበል መቆም ይችላል፡፡ ነቢዩ ይህን ነገር ፈፅመውታልና፡፡ እንዲሁም መንገደኛ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ከርሱ ጋር ለመሳሳም (ለመተቃቀፍ) መቆም ይቻላል፡፡ ሶሃቦች ይህን ነገር ተግብረውታልና፡፡ ነቢዩ ማንንም ሰው በመጥፎ ነገር አይቀበሉም(ማንንም ሰው በሚጠላው ነገር አያስበረግጉም ) ፡፡በሽተኛ ይጠይቃሉ ፣ ድኾችን ይወዳሉ ከሚስኪኖች ጋር ይቀመጣሉ ፣ሲሞቱ በቀብራቸው ላይ ይገኛሉ ፣ድኻን በድህነቱ አያንቋሽሹም ፣ንጉሥን በንጉሥነቱ አይፈሩም ነበር፡፡ የአላህን ፀጋ ቢያንስም እንኳ (በጣም ዝቅተኛ እንኳ ቢሆን )ያጋንናሉ(ትልቅ ደረጃ ይሰጡት ነበር)፡፡ከጣማቸው ይመገባሉ፣ አሊያም ይተውታል እንጂ ምግብ በፍጹም ንቀው አያውቁም፡፡ የሚበሉትና የሚጠጡት በቀኝ እጃቸው ብቻ ነበር፡፡ ሲጀምሩ ‹‹ቢስሚላህ ሲጨርሱ ደግሞ ‹‹አልሐምዱ ሊላህ›› በማለት ነበር፡፡ ጥሩ ሽታ ያላቸውን ነገሮች ይወዳሉ ፡፡እንደ ቀይና ነጭ ሽንኩርት ያሉ መጥፎ ጠረን (ሽታ)ያላቸውን ነገሮች ይጠላሉ ፡ ነቢዩ በአለባበሳቸውም ሆነ በአቀማመጣቸው ከሶሃቦች (ከባልደረቦቻቸው) ፈፅሞ አይለዩም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ተራው ዐረባዊ ይገባና ሙሐመድ የሚባለው ማንኛችሁ ነው? ይል የነበረው፡፡ ይበልጥ የሚወዱት የልብስ ዓይነት ቀሚስ( ጀለቢያ) (ከቁርጭምጭሚት በላይ ከባት ግማሽ ላይ የሚቀር ረዥም ልብስ ) ነው፡፡በአመጋገብም ሆነ በአለባበስ ከተፈላጊው በላይ አያባክኑም ነበር፡፡ ኮፊያና ጥምጣም ይብሳሉ፡፡ከብር የተሰራ ቀለበት በቀኝ እጃቸው ትንሽ ጣት (ኺንሲር ከምትባለው) ላይ ያደርጋሉ፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ እጅግ በጣም በርካታና ትልቅ የሆነ ፂም አላቸው፡፡