ቁርአን

ስለ ነቢዩ (ሱ.አ.ወ)ትሕትና እና አዳባቸው

ከማንም ሰው ይበልጥ አዛኝ ፣ከሁሉም ይበልጥ ባልደረቦቻቸውን አክባሪ፣ የተቀመጡበት ቦታ ከጠበባቸው እንዲሰፋ አድራጊ፣ ማንኛውንም ሰው በሚያገኙት ጊዜ አስሰላሙ አለይኩም በማለት የሚጀምሩ ነበሩ፡፡አንድን ሰው በእጃቸው ከጨበጡት የጨበጡት ሰው ራሱ እጁን እስካልሰበሰበ ድረስ እሳቸው እጃቸውን አይሰበስቡም ነበር ነቢዩ ሙሀመድ ለየት ያለ የሆነ ትሕትና(ተዋዱዕ) ባለቤት ነበሩ፡፡ ሰዎች ከተቀመጡበት ሲደርሱ እጫፍ ላይ ይቀመጡ ነበር እንጂ ሰዎችን አስነስተዉ አይቀመጡም ነበር፡፡በዚህ ነገር ላይ ሰዎችንም ያዙ ነበር፡፡ለተቀመጡት ሰዎች ሁሉ ድርሻቸውን ይሰጧቸው ነበር ፡፡ ከነቢዩ ጋር የተቀመጠ ሰው እንደርሱ ነቢዩ የሚያከብሩት ሰው ይገኛል ብሎ አያስብም ነበር፡፡ አንድ ሰው ከእርሳቸው ጋር ከተቀመጠ ይህ ሰው ካልቆመ በስተቀር እርሳቸው አይቆሙም ነበር፡፡ በጣም አሰቸኳይ ነገር ካጋጠማቸው ግን ፍቃድ በመጠየቅ ይቆማሉ፡፡ ነቢዩ ለራሳቸው ክብር ሰው ከመቀመጫው ተነስቶ መቆሙን ይጠሉ ነበር፡፡ አነስ ኢብኑ ማሊክ እንዲህ ብለዋል ‹‹ከአላህ መልእክተኛ ይበልጥ ባልደረቦቻቸው ዘንድ የተወደደ ሰው አልነበረም፡፡ ይሁን እንጂ ነቢዩ መምጣታቸውን ሲያዩ ተነስተው ለነቢዩ አይቆሙም ፡፡ይህም ነቢዩ ለራሳቸው ክብር ሰው ከመቀመጫው ተነስቶ መቆሙን እንደሚጠሉ ስለሚያውቁ ነው፡፡ (አህመድና ቲርሚዚ የዘገቡት ሐዲስ) (እንግዳ የመጣበት ሰው እንግዳን ለመቀበል መቆም ይችላል፡፡ ነቢዩ ይህን ነገር ፈፅመውታልና፡፡ እንዲሁም መንገደኛ ወደ ሀገሩ ሲመለስ ከርሱ ጋር ለመሳሳም (ለመተቃቀፍ) መቆም ይቻላል፡፡ ሶሃቦች ይህን ነገር ተግብረውታልና፡፡ ነቢዩ ማንንም ሰው በመጥፎ ነገር አይቀበሉም(ማንንም ሰው በሚጠላው ነገር አያስበረግጉም ) ፡፡በሽተኛ ይጠይቃሉ ፣ ድኾችን ይወዳሉ ከሚስኪኖች ጋር ይቀመጣሉ ፣ሲሞቱ በቀብራቸው ላይ ይገኛሉ ፣ድኻን በድህነቱ አያንቋሽሹም ፣ንጉሥን በንጉሥነቱ አይፈሩም ነበር፡፡ የአላህን ፀጋ ቢያንስም እንኳ (በጣም ዝቅተኛ እንኳ ቢሆን )ያጋንናሉ(ትልቅ ደረጃ ይሰጡት ነበር)፡፡ከጣማቸው ይመገባሉ፣ አሊያም ይተውታል እንጂ ምግብ በፍጹም ንቀው አያውቁም፡፡ የሚበሉትና የሚጠጡት በቀኝ እጃቸው ብቻ ነበር፡፡ ሲጀምሩ ‹‹ቢስሚላህ ሲጨርሱ ደግሞ ‹‹አልሐምዱ ሊላህ›› በማለት ነበር፡፡ ጥሩ ሽታ ያላቸውን ነገሮች ይወዳሉ ፡፡እንደ ቀይና ነጭ ሽንኩርት ያሉ መጥፎ ጠረን (ሽታ)ያላቸውን ነገሮች ይጠላሉ ፡ ነቢዩ በአለባበሳቸውም ሆነ በአቀማመጣቸው ከሶሃቦች (ከባልደረቦቻቸው) ፈፅሞ አይለዩም ነበር፡፡ ለዚህም ነው ተራው ዐረባዊ ይገባና ሙሐመድ የሚባለው ማንኛችሁ ነው? ይል የነበረው፡፡ ይበልጥ የሚወዱት የልብስ ዓይነት ቀሚስ( ጀለቢያ) (ከቁርጭምጭሚት በላይ ከባት ግማሽ ላይ የሚቀር ረዥም ልብስ ) ነው፡፡በአመጋገብም ሆነ በአለባበስ ከተፈላጊው በላይ አያባክኑም ነበር፡፡ ኮፊያና ጥምጣም ይብሳሉ፡፡ከብር የተሰራ ቀለበት በቀኝ እጃቸው ትንሽ ጣት (ኺንሲር ከምትባለው) ላይ ያደርጋሉ፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ እጅግ በጣም በርካታና ትልቅ የሆነ ፂም አላቸው፡፡

የጁሙዓ እና የጀማዓ ሶላት ትሩፋት

1. ነቢዩ እንዲህ ብለዋል፡-«ገላውን ታጥቦ ለጁሙዓ ሶላት የመጣ ሰው፣የተመቸዉን ያህል ሰግዶ ኢማሙ ኹጥባውን እስኪፈጽም ድረስ አዳምጦ ከኢማሙ ጋር ጁሙዓ የሰገደ ሰው እስከተከታዩ ጁሙዓ ድረስ ላለው (ኃጢዓቱ)እና ከተጨማሪ ሶስት ቀናት ጋር ምህረት (ከአላህ)ይደረግለታል፡፡ (ለሶላቱ ቀርቦ) አሸዋ እየነካካ የተጫወተ ሰው በእርግጥ ቁም ነገር የለሽ ነገር ሠርቷል፡፡»(ሙስሊም የዘገቡት ሐዲስ) 2. ነብዩ (ሰ.አ.ወ) እንዲሁ ብለዋለ፡-«ከግብረ ሥጋ ግንኙነት በኋላ በሚታጠበው ዓይነት ገላውን ታጥቦ ለጁሙዓ ሶላት የሄደ ሰው ግመል ለመሰዋት እንዳበረከተ ሰው ይቆጠራል ፡፡በሁለት ሰዓት ወደ ጁሙዓ የሄደ ሰው ላም እንዳቀረበ ይቆጠራል፡፡ በሶስት ሰዓት የሄደ ሰው ቀንዳም በግ እንዳቀረበ ይቆጠራል፡፡በአራት ሰዓት የሄደ ሰው ዶሮ እንዳቀረበ ይቆጠራል ፡፡ በአምስት ሰዓት የሄደ ሰው ደግሞ እንቁላል እንዳቀረበ ይቆጠራል ፡፡ ኢማሙ ብቅ ሲል መላይካዎች (የአላህን )ውዳሴ ለማዳመጥ በቦታው ይገኛሉ፡፡»(ሙስሊም የዘገቡት) 3. ነቢዩ እንዲሁ ብለዋለ ፡-«የኢሻን ሶላት በጀማዓ የሰገደ ሰው የሌሊቱን አጋማሽ(አላህን) በመገዛት እንዳሳለፈ ሰው ይቆጠርለታል፡፡ የሱብህን ሶላት በጀመዓ የሰገደ ሰው ደግሞ ሌሊቱን በሙሉ (አላህን በመገዛት) እንዳሳለፈ ሰው ይቆጠርለታል፡፡(ሙስሊም የዘገቡት ) 4. ነቢዩ እንዲሁ ብለዋለ ፡-«አንድ ሰው በጀማዓ የሚሰግደው ሶላት በቤቱና በሥራ ቦታው ከሚሰግደው ሶላት ከሃያ ሶስት እስከ ሃያ ዘጠኝ ባሉት ቁጥሮች ደረጃ ያህል ብልጫ አለው፡፡ይኸውም አንድ ሰው የተሟላ ውዱዕ አሳምሮ በማድረግ ለሶላት ብቻ የሚንቀሳቀስ እና ዓላማው ሶላት ብቻ ሆኖ ወደ መስጊድ ከመጣ በያንዳንዱ እርምጃ አንድ ደረጃ ከፍ የሚልና በዚያው ልክ ኃጢአቱ የሚሰረዝለት ቢሆን እንጂ መስጊድ እስኪደርስ ድረስ አንድም እርምጃ አይራመድም ፡፡ መስጊድ ሲገባም ሶላቱ እስከያዘው ድረስ ሶላት ውስጥ እንዳለ ሰው ነው የሚታሰበው፡፡ አንድ ሰው በሰገደበት ቦታ ላይ እስከ ቆየ ድረስ መላይካዎች አላህ ሆይ! እዘንለት፣ አላህ ሆይ! ምህረት አድርግለት ፣ አላህ ሆይ! ይቅር በለው እያሉ ጸሎት ያደርጉለታል ፡፡(ይህም)ሌሎችን ያላወከና ውዱዑን (ንጽህናውን)ካላፈረሰ ነው፡፡»(ቡኻሪና ሙስሊም የዘገቡተ ሐዲስ ሲሆን ቃሉ ከሙስሊም ዘገባ ነው)

የእስላም ማዕዘናት (አርካኑል እስላም)

የእስላም ማዕዘናት ማለት ሃይማኖቱ የታነጸባቸው የማዕዘን መሠረቶችማለት ነው። እነሱም ቀጥሎ በእብኑ ዑመር አማካይነት በተላለፈው ነቢያዊሐዲስ ውስጥ የተመለከቱት አምስት ማዕዘናት ናቸው። የኢስላም ማዕዘናት ነቢዩ ሙሀመድ እንዲህ ብለዋል፡- ኢስላም የተገነባው በአምስት መሰረቶች ላይ ነው፡፡ 1.ሸሃዳ፡-ከአላህ( በስተቀር) በእውነት ሊገዙት የሚገባ ጌታ የለም ብሎ መመስከር ማለት ከርሱ ውጭ በሰማያትም ሆነ በምድር በእውነት የሚያመልኩት አምላክ እንደሌለና ከርሱ ሌላ ያሉ አማልክት ሁሉ የሐሰት አማልክት መሆናቸውን መመስከር ነው፡፡ ነቢዩ ሙሀመድ መልዕክተኛው ናቸው በማለት እምነትን ማረጋገጥ 2. ሶላት፡-(የእስልምና ሁለተኛው መሰረት ነው የእስልምና ምሰሶ እንደሆነም ተረጋግጧል) በቀን አምስት ጊዜ ተደጋግሞ ይፈጸማል፡፡ ማዕዘናቶቿን ፣ደንቦቿን የጠበቀ ሆኖ ልቦናውን ለአላህ ፍፁም በማድረግ መስገድ (በወንጀልና በሰውየው መካከል ግርዶ ይሆናል)፡፡” 3.ዘካት፡-(ከተቀማጭ ሐብት በየዓመቱ ለድሆች መቋቋሚያ ይሆን ዘንድ መስጠት) ማንኛውም ሙስሊም ከወርቅ / 85 ግራም ያለው ከሆነ ከዓመት በኋላ ከመቶ 2.5 ለዘካ ወጪ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ማንኛውም ከወርቅና ከብር ውጭ ያለ ዘካ ወጪ የሚደረግለት ነገር የተገደበ የሆነ መጠን አለው፡፡ 4. ሐጅ፡- ወደተቀደሰችው የመካ ከተማ በመጓዝ ለአካለ መጠን የደረሰና አቅም ያለው ማንኛውም ሙስሊም ወደ ተቀደሰው መስጂድ መሄድ የሚችልበት መጓጓዣ ፣ መሄጃና መምጫ የሚሆነው ገንዘብ፣ ቀለብ ካለው መንገዱም ሰላም ከሆነ ሐጅ ማድረግ ግዴታ ይሆንበታል፡፡ 5.ሶውም(ጾም)፡- በየዓመቱ የረመዷንን ወር መፆም ፡፡አላህን በማምለክ አላማ ፆመኛ የሆነ ሰው ከኒያ(ከሃሳብ) ጋር ጠዋት ጎህ ከመውጣቱ(ከመቅደዱ) በፊት ጀምሮ ጸሐይ እስክትጠልቅ ድረስ ከምግብ ፣ ከመጠጥና ከግብረ ስጋ ግንኙነት(ከጾታዊ ግንኙነት ) ከሌሎችም ፆምን ከሚያበላሹ ነገሮች ታቅቦ መዋል ፣ራስን ከስጋዊ ፍላጎት ማቀብ ነው፡፡ ” (ቡኻሪና ምስሊም የዘገቡትሐዲስ)

00:00 / 00:00